1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትራንስፖርት ችግር እርዳታ ያላገኙት የጋምቤላ ተፈናቃዮች

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 22 2016

በጋምቤላ ክልል ጆር ወረዳ በታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከተፈናቀሉት መካከል አብዛኛዎቹ በመንገድ ችግርና በነዳጅ እጥረት ምክንት እርዳታ እንዳላገኙ ባለስልጣናቱ ተናገሩ፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው ጥቃት ከ7ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገልጧል፣ ታፍነው ከተወሰዱ 11 ህፃናት መካከል ደግሞ 7ቱ መመለሳቸውን የጋምቤላ ክልል አስታውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/4fMCG
Äthiopien | Straßenszene in Gambela
ምስል Negassa Desalegn/DW

በትራንስፖርት ችግር እርዳታ ያላገኙት የጋምቤላ ተፈናቃዮች

በጋምቤላ ክልል ጆር ወረዳ መጋቢት 26/2016 ዓም ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከተፈናቀሉት መካከል አብዛኛዎቹ በመንገድ ችግርና በነዳጅ እጥረት ምክንት እርዳታ እንዳላገኙ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው ጥቃት ከ7ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገልጧል፣ ታፍነው ከተወሰዱ 11 ህፃናት መካከል ደግሞ 7ቱ መመለሳቸውን የጋምቤላ ክልል አስታውቋል፡፡

በጋምቤላ ክልል አኙዋ ብሄረሰብ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡቶው ኡኮት ዛሬ ለዶቼ ቬሌ እንደተናገሩት በወቅቱ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳቶች ደርሰዋል፡፡ ከ7መቶ በላይ ቤቶች መቃጠላቸውንና ከ7ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ቀያቸውን ለቅቀው ተፈናቅለዋል ብለዋል፡፡ 11 ህፃናት ታፍነው ተወስደው እንደነበር ያመለከቱት አቶ ኡቶው እስከ ትናንት ድረስ 7ቱ መመለሳቸውን ገልፀዋል፣ እንስሳቱን ለማስመለስ የሚደረገው ጥረት ደግሞ እንደቀጠለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋድቤል ሙን የእርዳታ እህል ወደ ወረዳው ማዕከል መላኩን ተናግረዋል፣ “... እርዳታ ተልኳል፣ ያልሄደ አንዳንድ ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስ ነው፣ የምግብ እህል እርዳታን በተመለከተ በፌደራለ፤ ደረጃ ወደ 860 ኩንታል፣ በክልል ደረጃ 260 ኩንታል፣ ተገዝቶ ተልኳል፣) አተር ክክና ቦሎቄ ወደ ወረዳው ማዕከል ተልኳል፡፡” ነው ያሉት፡፡ ለመኝታና ለለመጠለያ  የሚፈለገው ሸራና ጅባ (ስጋጃ) መካኩንም ገልጠዋል፡፡

ሆኖም ባለው የመንገድ፣ የተሸከርካሪ፣ የጀልባና የነዳጅ እጥረት ምክንያት ወደ ተፈለገው የተፈናቃዮች አድራሻ ለማድረስ ለማድረስ እንዳልተቻለ አመልክተዋል፡፡ “ትልቁ ችግር ታች አንዳንድ ቀበሌዎች የመንገድ ችግር ስላለ፣ አንዳንድ ቦታዎች በጀልባ ነው የሚኬደው፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ጀልባም መኪናም አይደርስም፣ ትልቁ ችግራችን ህ ነው፣  ”

ጋምቤላ የጆር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኡመድ ኡባንግ እስካሁን ከተማ አካባቢ ያሉ 2ሺህ ያህል ተፈናቃዮች ብቻ እርዳታ ማግኘታቸውን ነው የገለፁልን፡፡ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለመድረስ የትራንስፖርት ችግር አጋጥሞናል ነው ያሉት፣ አንዳንድ እርዳታ ለማድረስ የሄዱ ተሸከርካሪዎችም በጭቃ ተይዘው እስካሁን እንዳልወጡ አስረድተዋል፡፡ የጀልባ ሞተርና የነዳጅ አቅርቦት እንዲቀርብ ጥያቄ አቅርው ምላሽ ከክልል  እየጠበቁ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ችገሮቹን ለማቃለልና እርዳታ ወደ ተጠቃሚዎቹ ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኡቶው ገልጠዋል፡፡

ጋምቤላ
ጋምቤላ ምስል Negassa Desalegn/DW

“ከተማ አካባቢ የተጠለሉ እርዳታ እየደረሳቸው ነው፣ ታች (ከወረዳ ማዕከል የራቁ አካባቢዎች) ያሉት የተወሰነ እርዳታ ነው የደረሳቸው፣ እስካሁን ከወረዳው ማዕከል ወደ ቦታው የተላከው 500 ኩንታል ብቻ ነው፣ የመንገድ ችግርና የጀልባ እጥረት አለ፣ አሁን ያለው የጀልባ ትራንስፖርት በአንድ ጊዜ ከ10 ኩንታል በላይ የማይጭን ነው፣ አሁን ከፍ ያለ ጭነት መያዝ የሚችል ጀልባ እየተፈለገ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

እንደ ዞኑ አስተዳደር መረጃ፣ መጋቢት 26/2016 ዓ ም በነበረው ጥቃት 61 ሰዎች ተገድለዋል፣ 14 ሰዎች ቆስለዋል፣ 738 ቤቶች ተቃጥለዋል፣ 7ሺህ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ 11 ህፃናት ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ 7ቱ ሰሞኑን ተመልሰዋል፣ 2ሺህ እንስሳት ደግሞ ተዘርፈው እስካሁን አልተመለሱም፡፡

ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ