1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓለም ዜና

Shewaye Legesseሐሙስ፣ ሚያዝያ 10 2016

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የልጃገረዶች ጠለፋ መባባሱ ተገለጠ። በክልሉ ኮሬ ዞን ውስጥ «እየተባባሰ መጥቷል» ባሉት ጠለፋ የተነሳ ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። ቡርኪና ፋሶ ሦስት የፈረንሳይ ዲፕሎማቶችን ከሀገር አባረረች። ፈረንሳይ ውሳኔውን አሳዛኝ ብላዋለች። የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች በሀገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው የተመድ አሳሰበ። ኢራን እስራኤል የኒኩሊየር ተቋሟ ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ በአጸፋው የእስራኤልን የኒኩሊየር መሰረተ ልማት ኢላማ እንደምታደርግ አስጠነቀቀች።

https://p.dw.com/p/4ewXO

ሀዋሳ፤ የልጃገረዶች ጠለፋ መባባስ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የልጃገረዶች ጠለፋ መባባሱ ተገለጠ። በክልሉ ኮሬ ዞን ውስጥ «እየተባባሰ መጥቷል» ባሉት ጠለፋ የተነሳ ሴት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል። በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ አስተማሪ የሆነ ቅጣት እንደማይሰጥ ያመለከቱት ወገኖች በአሁኑ ጊዜ ሴት ልጆች ወጥተው ለመግባት ስጋት እንደሆነባቸው ነው ለዶቼ ቬለ የተናገሩት። ስማቸው ያልተገለጸ አንድ አባት ከትምህርት ቤት የምትመለስ ልጃቸው በስድስት ወንዶች ከመንገድ መወሰዷን ነው የተናገሩት። ጉዳዩን በሕግ ለመፍታት ያደረጉት ጥረትም አለመሳካቱንም አመልክተዋል።

በተጠቀሰው ዞን በያዝነው ግማሽ ዓመት ብቻ ተጠልፈዋል የተባሉ የ24 ልጃገረዶች ሥም ዝርዝር ይፋ መደረጉን ተከትሎ ወላጆችና የህዝብ ተመራጮች በዞኑ የሕግ አካላት ላይ ጫና እያደረጉ መሆኑም ተገልጿል። በዞኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካ ሸዋንግዛው ወጋየሁ ከሀዋሳ በላከው ዜና አመልክቷል።

 

ኦጋዱጉ፤ ቡርኪና ፋሶ ሦስት የፈረንሳይ ዲፕሎማቶችን ማባረሯ

ቡርኪና ፋሶ ሦስት የፈረንሳይ ዲፕሎማቶችን ከሀገር አባረረች። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተባረሩት ዲፕሎማቶች «አፍራሽ እንቅስቃሴ» ባለው ምክንያት ከሀገር እንዲወጡ ማዘዙን አስታወቋል። ሦስቱ የፈረንሳይ ዲፕሎማቶች «የማይፈለጉ» መሆናቸው ተገልጾ በ48 ሰዓታት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለፈረንሳይ ኤምባሲ መልእክት ማስተላለፉም ተገልጿል። ውሳኔውን አሳዛኝ ያለው የፈረንሳይ መንግሥት በበኩሉ ዲፕሎማቶቹ የተባረሩት በመረጃ ባልተደረገፈ ጥርጣሬ ነው ብሏል። እርምጃው በቡርኪናፋ ፋሶ እና በቀድሞዋ ቅን ገዢ ፈረንሳይ መካከል የተፈጠረው ውጥረት መባባሱን እንደሚያመለክት አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።

 

ኒውዮርክ፤ የተመድ ደቡብ ሱዳን ምርጫ እንድታካሂድ መጠየቁ

 

የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች በሀገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው የተመድ አሳሰበ። የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ያስተላለፉት መልእክት የዘገየው የደቡብ ሱዳን ምርጫ በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2024 መካሄድ እንደሚኖርበት አመልክቷል። በሀገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ የነበረው እቅድ በፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር እና በተቀናቃኛቸው ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቻር ያላቋረጠ ጠብ ምክንያት መንቀሳቀስ አልቻለም። ለአምስት ዓመታት የዘለቀው የሁለቱ ተቀናቃኝ ሃይላት ውጊያም 400 ሺህ ሰዎችን ለሞት ሲያበቃ፤ ሚሊየኖችን ደግሞ ለመፈናቀል ዳርጓል። በጎርጎሪዮሳዊው 2018 ዓ,ም የሽግግር መንግሥት በመመስረት ለምርጫ መንገድ ያመቻቻል የተባለው የሰላም ስምምነት ተፈረመ። ሆኖም ኪርና ማቻር ምርጫው መደረጉን በሚመለከት ላይ የጋራ ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው ዓለም አቀፍ ታዛቢያዎች በመጪው ታኅሣሥ ወር የታሰበው ምርጫ መከናወኑን ይጠራጠራሉ። ሁኔታውን የመረመረው የመንግሥታቱ ድርጅት የደቡብ ሱዳን ተልእኮ ትናንት ይፋ ባደረገው ዘገባው ምርጫውን ለማካሄድ አስቀድመው መከናወን የሚኖርባቸው ዝርዝር ሂደቶች ገና እንዳልተነኩ አመልክቷል።  ደቡብ ሱዳን ራሷን የቻለች ሀገር ከሆነችበት ከጎርጎሪዮሳዊው 2011 ዓ,ም አንስቶ ምርጫ አላካሄደችም።

 

ቴህራን፤ የቀጠለው የኢራን ዛቻ

 

ኢራን እስራኤል የኒኩሊየር ተቋሟ ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ በአጸፋው የእስራኤልን የኒኩሊየር መሰረተ ልማት ኢላማ እንደምታደርግ አስጠነቀቀች። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት ኢራን ለሰነዘረችው ጥቃት የእስራኤል አጸፋ ሊከተል ይችላል በሚል የምትጠባበቀው የኢራን አብዮታዊ ዘብ የበላይ ለምላሹ ዝግጁ መሆናቸውን ዛሬ አስታውቀዋል። የእስራኤል ጦር ኃይል አዛዥ በበኩላቸው ለኢራን የአየር ጥቃት ምላሽ እንደሚሰጡ ዝተዋል። እንዲያም ሆኖ ጥቃቱ መቼ እና የት አካባቢ የሚለውን ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል። የኢራንን የኒኩሊየር ተቋም የሚጠብቀው ኃይል ሀላፊ አህመድ ሀግ-ሀታብ ጽዮናዊው መንግሥት ጥቃት ከሰነዘረ የማያወላውል ምላሻችንን ይጋፈጣል ማለታቸውን የፈረንሳይ የዜና ወኪል ዘግቧል። ኢራን እስራኤል ላይ በርካታ ሚሳኤሎችን በማስወንጨፍ ጥቃት ከሰነዘረች አንስቶ ሃገራት ቴል አቪቭ የአጸፋ እርምጃ እንዳትወስድ እየመከሩ ነው።  

 

ፍራንክፈርት፤ ጀርመን ለሩሲያ በመሰለል የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች መያዛቸው

የጀርመን ፖሊስ ለሩሲያ ሲሰልሉ ነበር ያላቸውን ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ። አቃብያነ ሕግ ተጠርጣሪዎቹ ለዩክሬን የሚደረገውን ወታደራዊ ድጋፍ በማቅለልም በአሜሪካ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ማቀዳቸውንም ዛሬ አመልክተዋል። ዲተር ኤስ እና አሌክሳንደር ጄ በሚል መጠሪያ የተገለጹት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በደቡብ ምሥራቅ ጀርመን ግዛት ባየርን፤ ባየሩዝ ውስጥ ትናንት መያዛቸውም ተገልጿል። ፖሊስ የተጠርጣሪዎቹን መኖሪያ ቤትና የሥራ ቦታም ፈትሿል። ግለሰቦቹ ከውጭ ሀገር የስለላ አገልግሎት ጋር «የከባድ ጉዳይ ስለላ» ተግባር ላይ በንቃት ይሠራሉ የሚል ጥርጣሬ መኖሩንም አዣንስ ፍራንስ ፕረስ በዘገባው ጠቁሟል። እንደ አቃብያነ ሕግ ገለጻም ዲተር ኤስ የተባለው ተጠርጣሪ ካለፈው ጥቅምት ወር አንስቶ ከሩሲያ የስለላ አገልግሎት ግንኙነት ካለው ግለሰብ ጋር መረጃዎችን ሲለዋወጥ ቆይቷል። ሌላኛው ተጠርጣሪም አብሮት የተያዘውን ግለሰብ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ሲያግዝ ነበረ ተብሏል።  

 

ዱባይ፤ ከመጠን ያለፈ ዶፍ ዝናብና ጎርፍ በባሕረ ሰላጤው ሃገራት

የአረብ ባሕረ ሰላጤ ሃገራት ከመጠን ባለፈ ዶፍ ዝናብ እና ጎርፍ መጥለቅለቃቸው እየተነገረ ነው። በተቃራኒው ኮሎምቢያ በድርቅ፣ የምዕራብ ባልካን አካባቢ ሃገራት ደግሞ ባልተለመደ መልኩ በዚህ ወቅት በረዶ እየዘነበ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። ላለፉት በርካታ ዓመታት ተመራማሪዎች ከመጠን ያለፈ የአየር ሁኔታ የሙቀት ማዕበል፣ ጎርፍ፤ ድርቅ፤ ወጀብ እና ሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ መገለጫዎች በተደጋጋሚ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ሲያሳቡ እንደነበር አሶስየትድ ፕረስ አስታውሷል። የሰሞኑን ተከታታይ ኃይለኛ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋ በማስመልከት የዜና ወኪሉ ዘጋቢ ሴት ቦረን ስታይን በተለያያዩ የዓለም ክፍሎች የተከሰተውን እንዲህ ገልጾታል።

«በመላው ዓለም የአየር ሁኔታው ያበደ መስሏል። ዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ በጎርፍ ተጥለቅልቋል፤ ኦማን በጎርፍ ተውጧል። ታንዛኒያም ውስጥ ጎርፍ ነው። ኮሎምቢያ ደግሞ ድርቅ በመሆኑ ቦጎታ ላይ ውኃ በራሽን ነው የሚታደለው። ባልካን አካባቢ በበረዶ ተውጧል። ሁሉ ነገር ከመጠን ያለፈ መስሏል።»

ዩናይትድ አረብ ኤሜሬት ከመጠን ያለፈው ዝናብ ካስተከተባት ጎርፍ ጋር እየታገለች ነው። በበረራዎች መዘግየትም በጎርፍ የተዋጠው የዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ ጉዟቸው የተረጋገጠላቸው መንገደኞች ብቻ እንዲመጡ ተማጽኗል።  የአውሮፕላን ማረፊያው ዋና ዋና የሚባሉ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ብቻ እንደሚያስተናግድ አስታውቋል። ከዚህም ሌላ መንገዶችም አሁንም በጎርፍ እንደተዋጡ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

 

ቡሩንዲ፣ በጎርፍ የተጎዳችው ቡሩንዲ እርዳታ መጠየቋ

ቡሩንዲ ለአንድ ወር የወረደው ከባድ ዝናብና ጎርፍ ላስከተለባት ጉዳት የእርዳታ ጥሪ አቀረበች። ቡሩንዲ ውስጥ በጎርፍ አደጋ ወደ አንድ መቶ ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። በምሥራቅ አፍሪቃ ባለፉት ሳምንታት የወረደው ኃይለኛ ዝናብ ታንዛኒያ ውስጥ ቢያንስ ለ58 ሰዎች፤ ኬንያ ደግሞ ለ13 ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑ ተገልጿል። የተመድ በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ የተጋለጡ ካላቸው 20 ሃገራት አንዷ ናት ባላት ቡሩንዲ ከመስከረም ጀምሮ ላልተቋረጠ ዝናብ መጋለጧን ይኽም በዋና ከተማዋ ጭምር ከባድ ጎርፍ ማስከተሉን አመልክቷል። የዝናብና ጎርፉ እስከያዝነው ወር ድረስ አለመቋረጥም የተፈናቃዮችን ቁጥር በ25 በመቶ ከፍ ማደረጉም ተገልጿል። የሀገሪቱ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ እንዲያውጅ ግፊት እየተደረገ ሲሆን ከ300 ሺህ በላይ ሕዝብ የሰብአዊ እርዳታ ፈላጊ ነው።  

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
Mittelmeer | Asylreform in der EU
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።